32
የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ የሃያ አንድ ቀን ጾም እና ጸሎት December 1 – December 21, 2017 ዓላማእግዚአብሔርን መፈለግ እና መንፈሳዊ ተሀድሶ በምዕመናን መካከል እንዲሆን መሪ ጥቅስ፦ ፈልጉኝ ታገኙኛላችሁኤር 2913

የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

  • Upload
    others

  • View
    14

  • Download
    1

Embed Size (px)

Citation preview

Page 1: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ

የሃያ አንድ ቀን ጾም እና ጸሎት

December 1 – December 21, 2017

ዓላማ፦ እግዚአብሔርን መፈለግ እና መንፈሳዊ

ተሀድሶ በምዕመናን መካከል እንዲሆን

መሪ ጥቅስ፦ “ፈልጉኝ ታገኙኛላችሁ” ኤር 29፤13

Page 2: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

2

Page 3: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

3

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ

የሃያ አንድ ቀን ጾም እና ጸሎት

December 1 – December 21, 2017

ዓላማ፦ እግዚአብሔርን መፈለግ እና መንፈሳዊ ተሀድሶ

በምዕመናን መካከል እንዲሆን

መሪ ጥቅስ፦ “ፈልጉኝ ታገኙኛላችሁ” ኤር 29፤13

በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ እግዚአብሔር ፈልጉኝ ይላል። ፈልጉኝ የሚለዉ

ደግሞ ልጆች ድብብቆሽ እንደሚጫወቱት ለማድከምና ላለመገኘት ሳይሆን በግልጽ

ለሚፈልጉት እነደሚገኝ በመናገር ነው። እንዲሁም በማቴ 7፤7 ላይ “ፈልጉ

ታገኛላችሁ፤ ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚፈልግ ያገኛል

የሚለምንም ይቀበላል የሚያንኳኳም ይከፈትለታል” ይላል። እግዚአብሔር

የሚያስፈልገንን የሚያዉቅ ነዉ። ነገር ግን “ፈልጉ” የሚለዉ ከእርሱ ጋር ሕብረት

እንድናደርግ ስለሚፈልግ ነዉ እንጂ የእኛን መድከም ስለሚፈልግ አይደለም ።

እግዚአብሔር በባህሪዉ ሩህሩህና ቸር አምላክ ነዉ ።

በእነዚህ ሃያ አንድ ቀናት የሚኖሩን የጸሎት አቅጣጫዎች ወይንም ትኩረቶቻችን

የሚከተሉት ናቸው።

- ምስጋናና አምልኮ ስለ ታላቅነቱ እና ስለ አደረገልን ነገር ሁሉ

- ንስሃ እና ራስን መመርመር “መልሰን ወደ አንተም እንመለሳለን” ሰቆ ኤር 5፤

21

- እዉነተኛ ተሀድሶ እና መመለስ

Page 4: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

4

- መንፈሳዊ መነቃቃት በቤተክርስቲያን እና በምዕመናን ሁሉ ላይ እንዲሆን

- የጥሞና/የዲቮሽን ህይወት በየግላችን እንዲበዛ

- ቤተክርስቲያንን የሚገዳደሩ ነገሮችን ጌታ እንዲመታ

- ቤተክርስቲያን በቀደመዉ ማንነቷ በታላቅ ጸጋና ሞገስ በዚህ ዘመን

እንድትቆም

- ወንጌል በኃይልና በስልጣን እንዲሰበክ… በተጣመም መንፈስ የሚሰብኩትን

ጌታ እንዲከለክል

- የምድሪቱን ጨለማ የሚገፍፍ መነቃቃት/ሪቫይቫል እንዲመጣ

- ፈሪሀ እግዚአብሔር በምዕመናን እና በአገልጋዮች ላይ እንዲጨመር

- በዚህ ዘመን የተነሳዉን ነገር ጌታ እንዲያጠራ

የሃያ አንድ ቀን ጾም እና ጸሎት አፈጻጸም

- የጸሎት አቅጣቻዎቻችን ከላይ የተዘረዘሩት ይሆናሉ። ሆኖም ግን ወቅታዊ

የሆኑ እና መንፈስ ቅዱስ በልባችን አክብዶ የሚያመጣቸዉ ጸሎቶች ካሉ

በየጊዜዉ ተጨማሪ ሆነዉ ይቀርባሉ።

- በየዕለቱ ከ10-15 ደቂቃ የሚሆን የቃል ጊዜ ይኖራል።

- ከቦታ ርቀት የተነሳ በዋናው ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን እንደ አመችነቱ

በየሰፈሩ ጾም ጸሎት ይደረጋል። ለምሳሌ በቫሊ፣ በኦሬንጅ ካዉንቲ፣

በኢንግልዉድ፣ በሳንታ ሞኒካ እና በፓሳዲና አና አካባቢዉ እንደ

አስፈላጊነቱ ይሆናል።

- ጾሙ ሰዉ እስከሚችለዉ ሰአት ይሆናል ሆኖም ግን ምሽት ከ6-8pm

የጸሎት ጊዜ ይኖረናል።

- ከሰኞ እስከ አርብ ድረስ በሁሉም ቦታዎች የምሽት የጸሎት ጊዜ ይኖራል።

ቅዳሜ ደግሞ እስከ 3 pm ድረስ ይሆንና እሁድ ሁሉም ቤተክርሰቲያን

ውስጥ እስከ አምልኮ መጨረሻ ግማሽ ቀን ብቻ ይሆናል ማለት ነዉ ።

Page 5: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

5

ጾም እና ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ

- መጽሐፍ ቅዱስ ጾም እና ጸሎትን እጅግ አድርጎ ያበረታታል። በጾምና ጸሎት

ብዙ በረከቶቸች እና ድሎች ታይተዋል። እግዚአብሔር አስደናቂ ነገሮችንም

ፈጽሟል። ጥቂቶቹን ብናነሳ…

- የንጉስ አዋጅ ተሽሯል። አስቴር ምዕራፍ 3 ንጉሱ በመቶ ሃያ ሰባት አገሮች

ላይ አይሁድ እንዲጠፉ ያወጀዉ አዋጅ የተሻረዉ እና የተገለበጠዉ በሶስት

ቀን ጾም እና ጸሎት ነበር ። እንዲሁም የነነዌ ከተማ ከኃጢአቷ የተነሳ

ትገለበጣለች ተብሎ ከተነገረ ወይም ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ህዝቡ በጾም እና

በጸሎት በአንድ ልብ ሲቀርቡ የወጣባቸዉ አዋጅ ተቀይሮ መትረፍ

ሆኖላቸዋል ።

- ሙሴ በዘጸ 32 አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በሲና ተራራ በቆየ ጊዜ ሲመለስ ፊቱ

ማየት እስከማይቻል ያበራ ነበር። በእርግጥም ከጌታ ጋር የቆየ ሰዉ ከዚህም

በላይ ሊሆን ችላል። ከእርሱ ጋር ቆይቶ እንዲሁ መመለስ አይቻልም።

ከእርሱ ጋር መቆየት ስናበዛ በሕይወታችን ላይ የሚሰሩ ስራዎች አሉ።

ሆኖም ግን በዚህ አመት በፊቱ በጾም እና በጸሎት እንዳንቆይ ብዙ

የምንሰጣቸዉ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን ምክንያቶች ሁሉ

አሸንፈን በጌታ ፊት በጾም ጸሎት መቆየታችን በሕይታችን ላይ ይሄ ነዉ

የማይባል ለዉጦችን ያመጣል።

- በአዲስ ኪዳንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርባ ቀንና ሌሊት በጾም ጸሎት

ቆይቷል። እንግዲህ ጌታ ጾም ጸሎት ካስፈለገዉ እኛማ እንዴት

አያስፈልገንም? ጌታ አገልግሎቱን የጀመረዉ ከጾም ጸሎት በኋላ ነዉ። ታዲያ

የእኛ አገልግሎት ያለ ጾምና ጸሎት እንዴት የተሳካ ወይንም የሰመረ ሊሆን

ችላል?

- እንዲሁም ሐዋሪያዉ ጳዉሎስ ብዙ ጊዜ ስለመጾም ተናግሯል። ያን ሁሉ

የሚያስደንቅ አገልግሎት ያገለገለዉ እንዲሁ ከልምዱ በመነሳት ሳይሆን

Page 6: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

6

ዕለት ዕለት ከሚያደርገዉ የጾምና የጾም ቆይታ የተነሳ ነዉ ። ሐዋሪያትም

ይሄ ልማድ እንደ ነበራቸዉ በሐዋ 13፤1-3 ላይ ይናገራል።

- እነዚህ እና ሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በብርቱ ጾም እና ጸሎት

አድርገዋል። ደግሞም ብዙ በረከት እና ድል አግኝተዋል ። ስለዚህ እኛም

ይህንን ፈለግ አብዝተን መከተላችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ

ለአገልግሎታችን ትልቅ በረከት ያመጣል።

ጾም ጸሎት ለምን?

ጾም ጸሎትን በተሳሳተ መንገድ ስንጠቀምበት ጾም ጸሎታችን ፍሬያማ አይሆንም።

መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳያስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፤ “ስለምን ጾምን? አንተም

አልተመለከትህንም ስለምንስ ሰዉነታችንን አዋረድን? አንተም አላወቅህም። እነሆ

በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ ሰራተኞቻችሁንም ታስጨንቃላችሁ” (ኢሳ

58፤3-4)። ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ። ነገር ግን የሚጾሙ የሚጸልዩት የጌታ ፈቃድ እና

ሀሳብ እንዲፈጸም ሳይሆን የራሳቸዉ ፈቃድ እና ሀሳብ እንዲፈጸም ብቻ ነበር።

ያዕቆብም በመልዕክቱ እንዲህ ብሏል “በምኞቶቻችሁ ትጸልያላችሁ እና አትቀበሉም።”

(ያዕ 4፤3) ይጸልያሉ ግን የሚጸልዩት በክፉ ተሞልተዉ ወይንም በስጋ ፈቃዳቸዉ

ተሞልተዉ ነበር። ጾም እና ጸሎት የእኛን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሳይሆን የጌታ ፈቃድ

በመካከላችን እንዲፈጸም የምንተጋበት መሳሪያ ነዉ።

ይሄን ነገር እየጻፍሁ አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። ኢትዮጵያ ዉስጥ አንዲት ትንሽ ከተማ

ዉስጥ አገለግል በነበረ ግዜ አንድ ወጣት ልጅ አንዲት በእርሱ እድሜ ያለች ወጣት

ሴት ወደደና ለጋብቻ ጠየቃት። እርሷ ግን ፈቃደኛ አልነበረችም። ፈቃደኛ

እንዳልሆነች ስትገልጽለት የሶስት ሳምንት ጾም ጸሎት ያዘ። ጾም ጸሎቱን ሲይዝ ጌታ

አንበርክኮ አንቀጥቅጦ በእጄ ያሰገባታል ብሎ በመዛት ነበር። ነገር ግን ከሶስት ሳምንት

ጾም እና ጸሎት በኋላ አነጋገራት። እርሷ ግን ፈቃደኛ አልነበረችም። ልጁ በዚህ

ምክንያት ለጥቂት ጊዜ ከጌታ ቤት አፈግፍጎ ነበር። ምክንያቱ የእርሱ ጾም ጸሎት

የጌታን እጅ ጠምዝዞ የራሱን ፈቃድ እና ምኞት መፈጸም ነበር እንጅ በትህትና ዉስጥ

Page 7: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

7

ሆኖ የጌታን ፈቃድ መፈለግ አልነበረም። ዛሬም በዘመናችን በጾም ጸሎት የጌታን እጅ

መጠምዘዝ እና ፍላጎቶቻቸዉ ብቻ እንዲሳካ የሚለምኑ አይጠፉም። ነገር ግን እንዲህ

መሆን የለበትም። ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ ጸሎትን ሲስተምራቸዉ “ፈቃድህ በሰማይ

እንደሆነች በምድር ትሁን ብላችሁ ጸልዩ” ነዉ ያለዉ (ማቴ 6፤9-13)።

ከፈሪሳዊነት እርሾ ተጠበቁ

ጾም ጸሎታችን ኃይማኖታዊ መሆን የለበትም። ኃይማኖታዊ ጾም ጸሎት ከጌታ ጋር

ንክኪ የሌለው ስርዓት ነው። በሉቃስ ምእራፍ 18 ላይ የሁለት ሰዎች ምሳሌ ይገኛል-

ፈሪሳዊዉ እና ቀራጩ። ፈሪሳዊዉ ሲጀምር ገና ሌላዉን በመናቅ እና በማንቋሸሽ

ነበር። ለምንድን ነዉ ሌላዉን መናቅ እና ማንቋሸሽ የጀመረዉ? ጸሎቱ የኃይማኖት

እንጅ የንክኪ አልነበረም። ምክንያቱም ከጌታ ጋር የቆየ ሰዉ በሌላዉ ላይ ፈራጅ

አይሆንም። በእርግጥ ከጌታ ጋር ንክኪ ቢኖረዉ ኖሮ ሌላዉን ሳይሆን እራሱን ነበር

የሚያየዉ ። በሌሎች ላይ የመፍረድ እና ራሳችንን ከሌሎች ጋር የማወዳደር መንፈስ

ከተሰማን ትክክለኛ መንፈስ ዉስጥ አለመሆናችንን መረዳት አለብን። መጾም እና

መጸለይ ብንችል እንኳ ከጌታ ጸጋ ስለበዛልን እንጂ ከራሳችን የሆነ አለመሆኑን

መረዳት አለብን። ከሆነዉ አንዳች ያለእርሱ አልሆነምና።

እዉነተኛዉ ጾም እና ጸሎት

1. በተለወጠ አእምሮ መጸለይ

የሮሜ ጸሐፊ ሲናገር በሮሜ 12፤1-2 “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንን አለም

አትምሰሉ”። ይህን ዓለም በሚመስል ማንነት ዉስጥ ሆነን የምንለምነዉ ነገር ሁሉ

ከዚህ ዓለም ነገር ጋር ብቻ የተገናኘ ይሆናል። በታደሰ እና በተለወጠ ማንነት ዉስጥ

ስንሆን ግን የእርሱን ፈቃድ እና እርሱን ደስ የሚያሰኘዉን እንጸልያለን። ዮሐ 15፤7

እንዲህ ይላል “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ለምኑ

ሆንላችሁማል።” እዚህ ጋ ሁለት ቁልፍ ቃላት አሉ፦ በእኔ ብትኖሩ እና ቃሎቼ

በእናንተ ቢኖሩ። ከእርሱ ጋር የተዋሃደ ሕይወት ስንኖር እና ቃሎቹ በእኛ ዉስጥ

ሲኖሩ እርሱ አስተሳሰባችንና አመለካከታችንን ሁሉ ያስተካክላል። እኛ በእርሱ ዉስጥ

Page 8: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

8

ከሆንን እና ቃሉም በሙላት በእኛ ዉስጥ ካለ ፍላጎታችን ጸሎታችን ሁሉ ከላይኛዉ

ወይንም ከቃሉ ጋር የተገናኘ ጸሎት ይሆናል ማለት ነዉ። ሕይወታችን በዚህ መንገድ

በሚቃኝበት ጊዜ የምንጸልየዉን ሁሉ እናገኛለን። ምክንያቱም ከፈቃዳችንና ከስጋ

ፍላጎቶቻችን የተነሳ ሳይሆን ከፈቃዱ ጋር የተገናኘ ጸሎት ማድረግ ጀምረናል ማለት

ነዉ። ስለዚህ በተለወጠ ማንነት የሚጸለይ ጸሎት ሁሉ ከጌታ ዘንድ መልስ

እንዲሚያገኝ ምንም ጥርጥር የለዉም።

2. ህብረት በማድረግና ወደ መገኘቱ በመግባት መጸለይ (Relationship)

ጾም እና ጸሎትን ስናስብ በመጀመሪያ ማሰብ ያለብን ታላላቅ ተአምራቶች እና

ድንቆችን ሳይሆን ከድንቅም በላይ ድንቅ የሆነዉ የእርሱን ፊት ወይንም ከእርሱ ጋር

መቆየትን ነዉ። የእርሱ ህልዉና ሲነካን የጸሎት ርእሳችንን እንኳ ሊያስጥለን ይችላል።

ከሁሉ በፊት የራብከኝ አንተ ነህ ፊትህን አብራልኝ በመገኘትህ አጥለቅልቀኝ ብለን

ወደ ፊቱ ስንቀርብ ነዉ ወደ እዉነተኛዉ የጌታ መገኘት ዉስጥ ስምጥ ብለን

የምንገባውና መዉጣት ወይንም ማቆም እስከማንችል ድረስ ወደ ፊቱ የምንገኘዉ።

በማቴ 17፣1-5 ኢየሱስ ሶስቱን ደቀ መዛሙርት ይዞ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ ያ ክብር

እና ህልዉና በመካከላቸዉ ሲመጣ ከዚያ መልቀቅ አልፈለጉም ነበር። ዛሬም ከሁሉ

በፊት እርሱ የሚያደርግልንን ነገሮች በማሰብ ሳይሆን እርሱን እራሱን በመፈለግ

ወደፊቱ እንቅረብ።

3. ጸሎት የአምልኮ ክፍል መሆኑን በማወቅ መጸለይ

ለሐዋሪያት ጾም እና ጸሎት ልማዳቸዉ ወይንም የአምልኮ ክፍላቸዉ ነበር ማለት

ይቻላል። ሐዋ 1፤14 በአንድ ልብ ሆነዉ በጸሎት ይተጉ ነበር። መቼም ጸሎት ሁለት

ነገሮችን ይጠይቃል፦በአንድ ልብ መሆንና መትጋት። በሐዋሪያት ህይወት ዉስጥ

ጾምና ጸሎት የአንድ ወቅት ጉዳይ ሳይሆን ሁልጊዜ የሕይወታቸዉና የአምልኮአቸዉ

ክፍል ነበር ማለት ይቻላል። “በሐዋሪያትም ትምህርት በህብረት እንጀራንም አብረዉ

በመቁረስ በጸሎትም ይተጉ ነበር” ሐዋ 2፤42። ጾም እና ጸሎትን ለችግር ማራገፊያ

ብቻ መፈለግ የለብንም። የአምልኮአችን ክፍልና ልማዳችን መሆን አለበት።

Page 9: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

9

አባቶቻችን በትጋት ይጸልዩ በነበር ጊዜ በመካከላቸዉ ብዙ ነገሮች ሆነዋል። ጾም

ጸሎትን በትጋት ያደርጉ በነበር ጊዜ የተከናወኑ ጥቂት ነገሮችን እናያለን፤

3.1. መንፈስ ቅዱስ ወረደ (ሐዋ 2፤1-4)

እዚህ ክፍል ላይ “ድንገት” የሚል ቃል አለ። እነርሱ የሚያዉቁት ጸልዩ መባላቸዉንና

በተስፋቸዉ መሰረት መጸለያቸዉን ነዉ። መንፈስ ቅዱስ መቼ እና በምን ሁኔታ

እንደሚመጣ፤ ሲመጣ ደግሞ እንዴት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያዉቁት ነገር

አልነበረም። ዛሬም ጾም እና ጸሎት የህይወታችን ክፍል ሲሆን እና በትጋት በደስታ

በፍቅር ስናደርገዉ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን እንደ ወደደ ይሰራል።

3.2. ጥርት ያለ የጌታ ድምጽ መጣ

እነዚህም ጌታን ሲያመልኩ እና ሲጾሙ መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳዉልን

ለጠራኋቸዉ ስራ ለዩልኝ አለ ሐዋ 13፡2። በዚያን ጊዜም ከጾሙ ከጸለዩ እጃቸዉንም

ከጫኑ በኋላ አሰናበቷቸዉ። በመካከላቸዉ የመጣዉ ድምጽ በማያሻማ ሁኔታ ነበር

የመጣዉ። ከመካከላቸዉ ማናቸዉም በዚያ ድምጽ የተጠራጠረ ወይንም ግራ የተጋባ

አልነበረም ። መቼም ጌታ ሲናገር በማያሻማ ሁኔታ ነዉ የሚናገረው። ነገር ግን ይህ

የሚሆነው ከጌታ ጋር ትኩስ የሆነ ንክኪ ያላቸዉ እና በትጋት ጾም እና ጸሎትን

በተገቢዉ ሁኔታ ለሚያደርጉ ሰዎች ነዉ።

3.3. የወህኒዉ መሰረት ተናወጠ የሁሉም እስራት ተፈታ

በሐዋ 16 በፊልጵስዮስ እስር ቤት ጳዉሎስ እና ሲላስ በነበሩ ጊዜ ሁኔታዉ እጅግ

ከባድ እና አስፈሪ አስጨናቂ ነበር። ነገር ግን እነርሱን ከአምልኮ እና ከምስጋና ጸሎት

አልከለከላቸዉም። በዚያ ሁኔታ ዉስጥ በእዉነት መዘመር ይቻላል ወይ ብለን ስናስብ

ጸሎት እና ጾም እንዲሁም አምልኮ ልማዳቸዉና የዘወትር ተግባራቸዉ የሆኑ ሰዎች

ከሆኑ ብቻ ናቸው በዚያ ሁኔታ ዉስጥ ማመስገን የሚችሉት። እዚህ ላይ እነ ጳዉሎስ

ጌታ ሆይ እባክህ የዚህን ወህኒ መሰረት አናዉጥ ብለዉ የጸለዩ አይመስለኝም።

Page 10: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

10

ሲያመልኩ ነዉ ተአምራት የሆነዉ። በጌታ መገኘት ዉስጥ ስንኖር የጸለይናቸዉን ብቻ

ሳይሆን ያልተጠባበቅናቸዉን በረከቶች እና ድሎችን ሁሉ እናገኛለን ።

4. በትህትናና የእርሱን ታላቅነት በማወጅ መጸለይ

እዉነተኛዉን ጾም እና ጸሎት ስናደርግ በእግዚአብሔር ፊት እራሳችንን እያዋረድን እና

ዝቅ እያደረግን መሆን ይኖርበታል። ጴጥሮስ በመልዕክቱ እንዲህ ብሏል። “እንግዲህ

በጊዜዉ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ራሳችሁን ከኃይለኛዉ ከእግዚአብሔር እጅ በታች

አዋርዱ” (1ኛ ጴጥ 5፤6)። ጴጥሮስ በነበረበት ዘመን ቤተ ክርስቲያን በታላቅ መከራ

ታልፍ ነበር። ከዚህም የተነሳ ብዙ የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ነበሩ። ነገር ግን ይህ

ከባድ እና አስጨናቂ ሁኔታ የሚታለፍበት መንገድ ነበረ። እርሱም እራስን

በእግዚአብሔር ፊት ማዋረድ እና በጸሎት ወደ ፊቱ መቅረብ ነዉ። ለዚህ ነዉ

የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት ብሉ የሚመክራቸዉ። መጣል

የሚቻለዉ እንዴት ነዉ ብለን ስናስብ መጣያዉ መንገድ ግን ጸሎት ይባላል።

የሚጸልዩ ሰዎች ናቸዉ ከባድ መከራዎችን ማለፍ የሚችሉት፦ መፍትሄ እግዚአብሔር

ጋ አለና። ጳዉሎስም ሲናገር አባትነት ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ ይላል

ኤፌ 3፤14። ለኤፌሶን ሰዎች በጸሎት ሲጋደል አባትነት ከሚሰየምበት ከአብ ፊት

እንደሚበረከክ ነዉ የሚናገረዉ። መጀመሪያ ይህን ሊያደርግ ለሚችለዉ ለአባታቸን

እዉቅና ይሰጣል። የተንበረከክነዉ በአብ ፊት አንደሆነ ስናስብ በእምነት እና በድፍረት

እንሞላለን።

እነዚህን የሚያክሉ ነገሮች ስለ ጸሎት ካነሳን ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በየቀኑ ትኩረት

ሰጥተን ልንጸልይባቸዉ ስለሚገቡ ነገሮችን ዘርዘር እያደረግን እናያለን::

አንደኛ እና ሁለተኛ ቀን :- ምስጋና እና ዉዳሴ

Page 11: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

11

የንባብ ክፍል፦ መዝ 150

እግዚአብሔርን ለማወደስ ሆነ ለማድነቅ ከታላቅነቱ መጀመር አለብን። ዳዊት

በመዝሙሩ የምስጋና እና የአምልኮ ጥሪ ያደርጋል። ለምን ማመስገን እንዳለብንም

ይናገራል። ስለችሎታዉ፣ ስለታላቅነቱ፣ ስለአምላክነቱ በሁሉም የሙዚቃ መሳሪያ ሁሉ

ማመስገን አለብን ይላል። ጌታ ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረው ጸሎት

‘በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ ብለዉ እንዲጀምሩ ነዉ የነገራቸዉ።

ወደ እግዚአብሔር ቅድስናና ህልዉና ይዞን የሚገባ ነገር ቢኖር ምስጋና አምልኮ ነዉ።

ብዙ ጊዜ ሀሳባችን እና ሁለንተናችን በምድራዊ ነገር ተይዞ እያለ ወደ እግዚአብሔር

ክብር መግባት እንፈልጋለን። ይሄ ግን ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። ወደ እርሱ መገኘት

እና ክብር የሚወስደን እርሱን በታላቅነቱ እና በማንነቱ ስናደንቀዉ ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- እግዚአብሔርን ስለ ታላቅነቱ ማመስገን

- ስለ ኃይሉ ችሎት እርሱን ማድነቅና ስለ ፍጥረቱ እንዲሁም ስለ እጆቹ ስራ

ማወደስ

- ስለ ድነታችን ማመስገን (ኤፌ 2፤1)

- ስላገኘናቸዉ መንፈሳዊ በረከቶችና አይኖቻችንን ስለተከፈተ ማመስገን

- እንዲሁም ወቅታዊ የጸሎት ጉዳዮች ላይ እንጸልያለን

ሶስተኛ ቀን፦ ስለተደረጉልን ነገሮች ጌታን ማመስገን

የንባብ ክፍሎች፦ 1ኛ ተሰሎ 5፤17-18፣ ፊል 4፤4-7፣ ኤፌ 5፤20፣ መዝ 105፤

10፣ መዝ 107፤43

Page 12: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

12

እግዚአብሔርን በጌትነቱ እና በማንነቱ ከማመስገን ባለፈ ሁኔታ ደግሞ ስላደረገልን

ነገሮች ጌታን ማመስገን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነዉ። ጳዉሎስ ሲናገር “ስለማይነገር

ስጦታዉ እግዚአብሔር ይመስገን” ይላል (2ኛ ቆሮ 1፤15)። በአዲሱ ትርጉም “ተዘርዝሮ

ስለማያልቅ ስጦታዉ እግዚአብሔር ይመስገን” ይላል። እዉነት ነዉ የእግዚአብሔር

ስጦታ ከቁጥር በላይ ነዉ። ከእርሱ ያልተቀበልነዉ ምን አለ? በረከቶቻችንን

እየቆጠርን ስናመሰግን ያልተደረገ ብለን የምናስበዉ ነገር እንኳን በጣም ያንስብንና

ምናልባትም በጥያቄያችን ልናፍር እንችላለን። የእግዚአብሔር ቃል በረከቶቻችንን

እንድንቆጥርና ውለታውን እንዳንረሳ ይመክረናል (መዝ 103፤2)። በእዉነት በመንፈስ

ተነክተን ባርኮታችንን መቁጠር ብንጀምር ምናልባትም ይሄ የሃያ አንድ ቀን ጊዜ

ላይበቃን ይችላል። ልመናዎቻችንን እንኳን ስናቀርብ ከምስጋና ጋር ማቅረብ አለብን።

ፊል 4፤4-7 “ልመናችሁን ከምስጋና ጋር አቅርቡ” ነዉ የሚለን። ስለዚህ እኛ ደግሞ

እንደ አማኝ ወይንም እንደ ዳነ ሰዉ ምስጋና የህይወታችን ክፍል ሊሆን ይገባዋል።

ስለዚህ ይህን ቀን በረከታችንን ዘርዘር አድርገን በመቁጠር እንጀምራለን።

አስታዉሳለሁ አንድ ጊዜ አዲስ አበባ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በነበርሁ ጊዜ

ወደ ህይወቴ አንዳንድ ችግሮች መጥተው ነበር። ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ለመጸለይ ከግቢ

ወጣን። ለሁለት ቀን ያህል ስንጸልይ ከዚያ ጓደኛዬ ጋር ጸሎታችንን በረከታችንን

በመቁጠር ጀመርን። በዚህ ጊዜ ወደ ልዩ አምልኮ ዉስጥ ገባን። ለጸሎት

የተገናኘንበትን ረሳነዉ። ዉስጣችን በምስጋና እና በአድናቆት ብቻ ተሞላ። መጨረሻ

ላይ አብሮኝ ለነበረዉ ወንድም የጸሎት ርዕሴን ትቼዋለሁ አልሁት። እሰከ

መጨረሻዉም የጸሎት ርዕሱ ሳይነሳ በምስጋና አለቀ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

ምስጋና…

- ጌታ ስላደረገልን ነገር ሁሉ

- በጤንነት መዉጣት መግባት ስለባረከን

- የምናመልክበት አዳራሽ ስለሰጠን

Page 13: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

13

- በመካከላችን ስላለዉ ፍቅር እና መተሳሰብ

- በዚህ ዓመት ስለዳኑ ጥቂት ሰዎች

- በስርጭት ጣቢያዎች ስላለዉ የወንጌል ስራ

- በየአገልግሎት ዘርፉ የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ጌታ ስለሰጠን እንዲሁም ስለ

መሪዎቻችን

- ዓመቱን በሙሉ የጌታ ጥበቃ በዝቶልን በድል ስላጠናቀቅን

- በዚህ አመት ስለተወለዱ ህጻናትና ታመዉ ስለዳኑት ቅዱሳን

- ለፓራዳይም አገልጋይ ስለሰጠን

አራተኝ ቀን፦ ንስሃ ሰለ ግል ኃጢአታችን

የንባብ ክፍል ሮሜ 3፤11-21፣ ኢሳ 1፤18፣ ማቴ 4፤17፣ ሉቃ 24 ፤44-48፣

ሉቃ 5፤31-32

ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ፣ ተሃድሶም ሆነ መነቃቃት የሚባሉ ነገሮች ሁሉ

የሚጀምሩት እዉነተኛ ንሰሃ በእግዚአብሔር ፊት ስንገባ ብቻ ነዉ። ራሳችንን

መመርመር እና ንስሃ መግባት የመንፈሳዊነት ምልክት ነዉ እንጂ የኃጢአተኛነት

ምልክት አይደለም። በአሁኑ ሰአት ንሰሃ መግባትና ስለ ኃጢአት መጸጸትና ማልቀስ

ከመካከላችን የራቁ ነገሮች ናቸዉ። በእዉነት ኃጢአት ስለማይሰራ ነዉ የማንጸጸተዉ

እና የማናለቅሰዉ ወይስ የድንዛዜ እና ኃጢአትን የመልመድ ምልክት ነዉ? ኢየሱስ

በማቴ 5፤4 ሲናገር “የሚያዝኑ ብጹአን ናቸዉ” ይላል። ይህ ማለት ስለ ኃጢአታቸዉ

የሚጸጸቱ የሚያለቅሱ ማለት ነዉ። ምክንያቱም ጳዉሎስም በሁለተኛ የቆሮንቶስ

መልዕክቱ ላይ እንዲህ ይላል “ስላዘናችሁ ደስ ብሎኛል” ይላል። ይህንንም የሚለዉ

በኃጢአታቸዉ ማዘናቸዉንና መጸጸታቸዉን ነዉ። የስጋ ደዌ በሽታ ያለባቸዉን ሰዎች

ገላቸዉን እሳት ቢያቃጠላቸዉም የማይሰሙት ለምንድን ነዉ ቢባል ሰዉነታቸዉ ስለ

Page 14: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

14

ደነዘዘና ስለማይሰማቸው ነው። በአካባቢዉ ያሉ ሴሎች ስለሞቱ ምንም ነገር

አይሰማቸዉም። ዛሬም ኃጢአት እያደረግን የማይሰማንና የማንጸጸት ከሆነ

ምናልባትም በመንፈሳችን ሞተን ወይንም ደንዝዘን እንዳይሆን ብዬ እፈራለሁ።

ስለዚህ ንስሃ መግባትና የግል ሕይወታችንን መመርመር አስፈላጊ ነገር ነዉ።

እግዚአብሔር በኢሳ 1 ላይ ኑና እንዋቀስ ይላል። ይህን ማለቱ ሊያነጻን ሊቀድሰን ነዉ

እንጅ ሊፈርድብን አይደለም። 1ኛ ዮሐ 1፤7 8 “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን

እናስታለን እዉነትም በእኛ ዉስጥ የለም” ይላል። ኃጢአታችን ብንናዘዝ ግን

ከኃጢአታችን ሊያነጻን የታመነ እና ጻድቅ ነዉ።

ኃጢአት እንዳለብን እያመንን ከኃጢአታችን ብንናዘዝ ከኃጢአታችን ሊያነጻን የሚችል

ኃይል ያለዉ ትኩስ ደም ዛሬም አለ። “ከኃጢአት ሁሉ ያነጻል” እንደሚል ቃሉ።

ስለዚህ ንሰሀ ለመግባት መሸማቀቅ የለብንም። የክርስቶስ ደም ድፍረት ሊሆነን

ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ በአንደኛ ዮሐንስ መልዕክት ሲናገር “ኃጢአትን አታድርጉ”

ካለ በኋላ “ብትሰሩ ግን ጠበቃ ቆሞላችኋል” ነዉ የሚለን። ኢየሱስ ጠበቃችን ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

ንሰሃ…

- በየእለቱ በእግዚአብሔር ፊት ስለምንበድላቸው በደሎች

- እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ ስላላከበርነዉ

- በብዙ ኃጢአት ተከበን እያለ እንደ ንጹህ ስለ ማስመሰላችንና ስለ

ግብዝነታችን

- ለአገልግሎት እና ለመንፈሳዊ ሕይወት የሰጠነዉ ዋጋ አናሳ ስለመሆኑ

- የእግዚአብሔርን ስራ በቸልታ ስለመስራታችን

- ጥፋት እና ክፉ ነገር እያየን እንደሚገባ ስላለመጸለያችን

Page 15: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

15

አምስተኛ ቀን፦ ንሰሀ ስለቤተ ክርስቲያን

የንባብ ክፍል ኢዩኤል 1-2፣ ሰቆ 5፤1-21፣ ራዕ ምዕራፍ 2 እና 3

በግል ሕይወታችን እንደሚገባ ባልተመላለስንባቸዉ ነገሮች ላይ ንሰሀ መግባት

መጸጸት እና ማልቀስ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ቤተክርስቲያንም ከማንነቷ ወጥታ

እርሷን በማይመጥናት ኑሮ እና ሕይወት ስለመመላለሷ በእግዚአብሔር ፊት ንሰሀ

ልንገባ እና ልናለቅስ ይገባናል። “አቤቱ መልሰን እኛም እንመለሳለን ዘመናችንንም

እንደቀድሞዉ አድስልን” (ሰቆ ኤር 5፤21)። ኤርምያስ መልሰን የሚል ጩህት

ያሰማል። ሌሎቹም ነብያቶች የንሰሀ ጥሪ አድርገዋል። ኢዩኤል በምዕራፍ አንድ ላይ

ለሁሉም ማለትም ለካህናት፣ ለአባቶች፣ ሙሽሮቹን እንኳ ከጫጉላ ዉጡ፤ ሁላችን

ንሰሀ እንግባ ወደ እግዚአብሑር እንመለስ ይላል። ኢዩኤል የንሰሀዉን ምክንያት

ሲናገር በአምላካችን ቤት ሊኖር የሚገባዉ ነገር ጠፍቷል ይላል። ለምሳሌ ደስታ እና

እልልታ ጠፍቷል፤ ቁርባን ወይንም አምልኮ ጠፈውተዋል፤ ጎተራዎቹ ባዶ ሆነዋል

ይላል። በእግዚአብሔር ቤት ሊታዩ የሚገባቸዉ ነገሮች ሲጠፉ በእዉነት በጌታ ፊት

ንሰሀ መግባት ያስፈልጋል። ሰላም ደስታ እና እልልታ መገኛቸዉ በጌታ ቤት መሆን

ሲገባቸው በእግዚአብሔር ቤት ከጠፉ አሳዛኝ ነገር ነዉ። ዛሬም በጌታ ቤት ሊታዩ

የሚገባቸዉ እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ብቻ የሰጣት ነገሮች በቤተክርስቲያን

ዉስጥ መታየት አለባቸው። ካልታዩ ግን ምክንያቱ ምንድን ነዉ ብሎ መመርመር እና

መጸለይ ያስፈልጋል። ዛሬ ከእግዚአብሔር ቤት የጠፉ ነገሮች መመለስ አለባችው።

አምላካችን አልተለወጠም። ኢዩኤል በምዕራፍ 2 12-13 እንዲህ ይላል “አሁንስ ይላል

እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሀ በጾምም በለቅሶ እና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ።

ልባችሁን እንጅ ልብሳችሁን አትቅደዱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸር እና መሃሪ

ለቁጣ የዘገየ ምህረቱ የበዛ ለክፋትም የተጸጸተ ነዉና ወደ እርሱ ተመለሱ።” ንሰሀ

ዉጫዊ ነገር ሳይሆን ዉስጣዊ ነገር ነዉና ከልብ የሆነ ልቅሶ ወደ እርሱ ጩሁ፤ እርሱ

Page 16: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

16

ደግሞ መኃሪ አምላክ ነዉ፤ የማጥፋት ሳይሆን የመማር ፕሮግራም ነዉ ያለዉ ነው

ኢዮኤል የሚለን።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- በቤተክርስቲያን ዉስጥ ሊታዩ ስለሚገባቸዉ ነገሮች፤ ፍቅር ሰላም ደስታ

እንደሚገባ ስላልታዩና ቤተክርስቲያን የሚገባዉን ያህል ተልዕኮዋን

ስላልተወጣች ንስኃ መግባት

- ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ ነገሯ እየቀዘቀዘች ስለመምጣትዋ ንስኃ መግባት

- መንፈስ ቅዱስ የሚገባዉን ያህል ስፍራ ስላለማግኘቱ ንስኃ መግባት

- የገኃነም ደጆች አይችሏትም ተብሎ ሳለ በብዙ ነገር ስለማመቻመቿ ንስኃ

መግባት

- ሰዶማዊነትን የሚገባዉን ያህል ስላለመቃወሟና አንዳንድ ዲኖሚኔሽኖች

እጃቸዉን ለዚህ ክፉ ኃሳብ ለመስጠታቸዉ ንስሃ መግባት

ስድስተኛ ቀን፦ ንሰሀ ስለ ሃገር

የንባብ ክፍል ነህ 1፣ አሞጽ 4፣ ዳን 9

ሃገር፣ ቤተክርስቲያንና ቤተሰብ የተያያዙ ነገሮች ናቸዉ ። አንዱ ሲነካ ሁሉም ይነካል።

ቤተክርስቲያን ለተለየ ዓላማ ማለትም ለወንጌል ተጠርታ የወጣች ብትሆንም በዓለም

እስካለች ድረስ የሃገር ክፍል ናት። ሃገር ሲታመም አብራ ትታመማለች፣ ሃገር ሲደሰት

አብራ ትደሰታለች። ስለዚህ በሀገሪቱ ላይ ስለተሰራዉ በደል ንሰሀ መግባትና ማልቀስ፣

መሪዎችን ይቅር እንዲል መጸለይ መጾም ያስፈልጋል። ዳንኤል በምዕራፍ 9 ላይ

ስላባቶችና ስለ ሃገር ንሰሀ ገብቷል። ነህምያ በምዕራፍ አንድ ምንም እንኳ መንፈሳዊ

ተልዕኮ ቢኖረዉም ለሃገር አልቅሷል፤ ንስሀ ገብቷል ። ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ እና

Page 17: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

17

በምንኖርባት በዚህች ምድር በመሪዎች የተሰሩ ግፎች እና በደሎችን፤ የደሀ አደጎችን

መበደል ስለ እነእርሱ በእግዚአብሔር ፊት ንሰሀ እየገባን እንጸልያለን።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- እግዚአብሔር ከድሮ ጀምሮ በነበሩ መሪዎች ለተሰራዉ ግፍ ምህረት

እንዲያደርግ

- የሃገር መሪዎች ስላደረጉት ጥንቆላ እና የጣኦት አምልኮ

- መሪዎች ድሆችን በመበደል ስላስጨነቋቸዉ

- በህዝቡ እና በመሪዎች መካከል መከባበር ስለመጥፋቱ

- በጎሳዎች ወይንም በህዝቦች መካከል ስላለዉ መናናቅ እና መከፋፈል

እግዚአብሔር ይቅር እንዲል

- በዚህ ዘመን ያሉ መሪዎች ለብዙ ክፉ ነገርና ኃጢያት ስለመጨመሩ

ምክንያት ስለ መሆናቸዉ

ሰባተኛ ቀን፦ ተሃድሶ በግል ሕይወት

የንባብ ክፍል ኤፌ 5፤14-20፣ ሉቃ 24 በሙሉ

መቼም መታደስ የሚኖረዉ መጀመሪያ የፈረሰ ነገር መኖሩን ስንቀበል ብቻ ነዉ። ዛሬ

በግል ህይወታችን በብዙ አቅጣጫ የፈራረሱ ነገሮች አሉ ብለን እናምናለን። ብዙ

የጥሞና ጊዜ ከቃሉ እና ከጌታ ጋር በጸሎት ማሳለፍ እየፈራረሱ ካሉ ነገሮች አንዱ

ነዉ። ምዕመናንም ሆነ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በጌታ ፊት ከሚያሳልፉት ጊዜ ይልቅ

በዩቱዩብ የሚያሳልፉት ጊዜ እንደሚበልጥ ምንም ጥርጥር የለዉም። አገልጋዮች

ማለትም ፓስተሮች እና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በአማካኝ ስምንት ደቂቃ በቀን ብቻ

ነዉ የሚጸልዩ የሚል መረጃ አለ። ከሳምንት እስከ ሳምንት መጽሐፍ ቅዱሳቸዉን

Page 18: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

18

የማያነቡ እና በጌታ ፊት ለጸሎት የማይቀርቡ ምእመናን ቁጥር ይሄ ነዉ የማይባል

ነዉ። ራስ ወዳድነትና እግዚአብሔርን መዳፈር (የድፍረት ኃጢአት) ወደ

ቤተክርስቲያን ከገቡ ሰንብተዋል። እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች በሕይወታችን

መታየታቸዉ የማያስደነገጡ እና የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል። ስለዚህ ተሃድሶ

አያስፈልገንም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ወይንም ልበ ደንዳናነት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ከዚህ ጾም ጸሎት በኋላ አንዱ የሚጠበቀዉ ዉጤት በእያንዳንዳችን ላይ የግል የጥሞና

ጊዜያችን ማለትም ከቃሉ እና በጸሎት ከጌታ ጋር የምናሳልፈዉ ጊዜ እንዲጨምር ነዉ

። ሰሞናዊ እንዲሆን ሳይሆን ልማዳዊ እንዲሆን ነው።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- የግል የጥሞና ጊዜያችን እንዲታደስ

- ከቃሉ በጸሎት የምናሳልፈዉ ጊዜ የበዛ እንዲሆን

- መንፈሳዊ እይታዎቻችን እንዲጨምሩ

- ፈሪሀ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንዲጨምር

- ለእግዚአብሔር ቤት እና ለአገልግሎት ያለን አመለካከት እንዲለወጥ

- የቤተሰብ አምልኮ እንዲታደስ፣ ወላጆች ከልጆች ጋር ቋሚ የሆነ የአምልኮ

እና የጸሎት ጊዜ እንዲኖራቸው

- ልጆችን እንደሚገባ ጌታን በማሳየት መምራት እንዲሆን፤ መመቻመች

እንዲወገድ፤ ጌታን ማሳየት እንዲሆን

ስምነተኛ እና ዘጠነኛ ቀን፦ ተሃድሶ ለቤተ ክርስቲያንና ለሃገር

የንባብ ክፍል ነህ 1 እና 2

Page 19: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

19

በእርግጥ የግል ሕይወታችን ታደሰ ማለት ቤተ ክርስቲያን ታደሰች ማለት ቢሆንም

ቤተክርስቲያን ደግሞ የፈራረሱባት እና ከጣለቻቸዉ ነገሮች መታደስ እና ወደ

ቀደመዉ ክብሯ እና ማስፈራራቷ እንዲሁም ሞገሷ መመለስ እና መታደስ

ያስፈልጋታል። ነህምያ ጠጅ አሳላፊ በነበረ ጊዜ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ፣ በሮቿ

መቃጠል፣ ቅሬታዎች በታላቅ ጉስቁልና መኖር ሲሰማ ነገሩን በቸልታ እና

በግድየለሽነት አላየዉም። ይህን ጉዳይ በእግዚአብሔር ፊት ይዞት ነበር የቀረበው።

ለአያሌ ቀን አንድ እና ሁለት ከሚባል ባለፈ ቁጥር በጾም ጸሎት ይዞት ቀረበ።

ነህምያም በዚያ ጾም ጸሎት ዉስጥ ያገኘዉ ነገር ቢኖር በንጉስ ፊት ሞገስ ነበር።

የፈለገዉን እስኪሰጠዉ ድረስ ነበር ሞገስን ያገኘዉ። እንዲሁም እግዚአብሔር ነገሩን

እንዴት እንደሚፈጽመዉ ጌታ ትክክለኛ ምሪት ሰጠዉ። በልቡ የገባዉ ሸክም በዚህ

ጾም ጸሎት ምክንያት ተፈጸመ። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን የምናያቸወ ጉድለቶችም ሆነ

እንደሚገባ አለመሆን ተግተን ከልብ ከሸክም በመነጨ ሁኔታ በእግዚአብሔር ፊት

ብንቀርብ አምላካችን መልስ የሚሰጥ እንዲያዉም እርሱ መልስ የሆነ አምላክ ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- ቤተክርስቲያን ክብሯ እና ሞገሷ እንዲመለስ። “ታላቅ ጸጋ ነበረባቸዉ” ሐዋ

ምዕራፍ 2

- የእርስ በእርስ ፍቅር እና መከባበር እንዲታደስ። ኢየሱስ በዮሐ 13፤31

“በፍቅሬ ያዉቋችኋል” ነዉ የሚለዉ። ፍቅራችን በዉጭ ያሉትን እንዲስብ

- ጋብቻ እንዲከበርና የትዳር ህይወት እንዲታደስ። ዛሬ የሚፋቱ ክርስቲያኖች

ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ አማኞች ሲፋቱ ምንም አይመስለንም።

- ቤተ ክርስቲያን የገሃነም ደጆች አይችሏትም እንደተባለ የምታስፈራ እና

ለጨለማዉ መንግስት ችግር እንድትሆን

- በአማኞች መካከል ያለዉ መናናቅ እና ጥላቻ በፍቅር እንዲለወጥ

- አገልጋዮች ወንጌልን እየሸቀጡ ለራስ ጥቅም በማዋል ላይ ስላሉ

እግዚአብሔር ከእንዲህ አይነቱ ተግባር እንዲመልሰን

Page 20: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

20

- ወንጌልን አባቶቻችን በሰበኩበት መንፈስ እንድንሰብከዉ (2ኛቆሮ 2፤1-5)

ዘጠነኛ ቀን፦ ተሀድሶ ለምድር ወይንም ለሃገር

የንባብ ክፍል አስቴር 8

ዳዊት በመዝሙረ ዳዊት 104፣30 መንፈስህን ትልካለህ የምድርንም ፊት ታድሳለህ

ይላል። ተሃድሶ የሚያስፈለገን ሰዎች ብቻ አይደለንም። የጌታ መንፈስ ሰዉን ብቻ

ሳይሆን ምድርን ያድሳል። ምድር ስትታደስ የሚገባዉን ፍሬ ትሰጣለች።

በእስራኤላዊያን መካከል ይሄ ነገር የተለመደ ነበር። እነርሱ ሲመለሱና ነገራቸዉን

ከእግዚአብሔር ጋር ሲያስተካክሉ ምድራቸዉና እርሻቸዉ ብዙ ፍሬ ያፈራ ነበር ።

ነገራቸዉ ሲበላሽ ደግሞ አብሮ የምድራቸዉም ጉዳይ ይበላሽ ነበር። አንዳንዴ

ምድሪቱ ፍሬ አታፈራም ብታፈራ ደግሞ ሰብሉን ተምች እና ደጎብያ ይበላዉ ነበር ።

ስለዚህ ለምድርም ለህዝብም ተሀድሶ አስፈላጊ ነገር ነዉ ማለት ነዉ። አስቴር ደግሞ

ስለ ህዝቧ እንዲህ አለች “እኔ በህዝቤ ላይ የሚወርደዉን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት

እችላለሁ ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ (አስቴር 8፤6)።

ሙሴም ስለ ህዝቡ እንዲህ ብሎ ጸልዮአል፤ “ይህን ህዝብ ከምታጠፋ እኔን ከህይወት

መዝገብ ደምስሰኝ” ብሏል። እኛም ዛሬ በምንኖርባት ምድርም ሆነ በሃገራችን

የሚሆነዉን እያየን ችላ ማለት የለብንም።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- እግዚአብሔር ምድራችን እንዲያድስና ፍሬ እንድታፈራ

- ይህች ምድር የጣለችዉን መንፈሳዊ ነገር እንድታነሳ

- እግዚአብሔርን ስታስቀድም የነበረች ምድር ዛሬ እግዚአብሔርን የመጨረሻ

እያደረገች ነዉና አምልኮተ እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ እንዲታደስ

Page 21: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

21

አስረኛ ቀን፦ የእግዚአብሔር ክብር በመካከላችን እንዲሆን

የንባብ ክፍል ኢሳ 6፤1-6፣ መዝ 15፤1-7፣ 1ኛ ነገ 19፤19-20

ኢሳያስ ንጉስ ኦዝያን በሞተበት አመት አንድ አስደናቂ ነገር በሕይወቱ ላይ ተከናወነ።

እርሱም እግዚአብሔርን ማየቱ ነበር። ኢሳያስ ከዚያ በፊትም አገልጋይ ነበር። ትንቢት

ይናገር ነበር። ያን ቀን ግን እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ ወደ ኢሳያስ መጣ።

እግዚአብሔርን ባየዉ ጊዜ በመጀመሪያ ጠፍቻለሁ ወዮልኝ ነዉ ያለዉ። ከንፈሬ

የረከሰበኝ ሰዉ ነኝ ነዉ ያለዉ (ኢሳ 6፤1-6)። የጌታ ክብር ሲገለጥ ወይንም

እግዚአብሔር በልዩ መገኘቱ ሲመጣ የሚሆነዉ ነገር እዉነተኛ ትህትናና ራሳችንን

ማየት ነው። በእግዚአብሔር ክብር እና ህልዉና የተነካ ሰዉ ወደ ተለየ ልምምድ

ዉስጥ ይገባል እንጅ እንደ በፊቱ አይቀጥልም። ኤልሳዕ በእርሻ ላይ እያለ ኤልያስ ሄዶ

መጎናጸፊያዉን ጣለበት። በዚያን ጊዜ እርሻዉን አቁሞ ተከተለዉ። እርሱም እባክህ

እናት እና አባቴን እስማቸዉ ዘንድ ፍቀድልኝ አለዉ። እርሱም ምን አደረገሁህ መሄድ

ትችላለህ አለዉ። ኤልያስ እባክህ ተከተለኝ አላለዉም። ጌታ በክብሩ ነክቶት ስለ ነበር

ኤልሳዕ እንደ በፊቱ እርሻዉ ላይ መቀጠል አልቻለም።

በሁሉም አቅጣጫ የጌታ ክብር እንዲገለጥ ልንጸልይ ያስፈልጋል። በጌታ መገኘት

ዉስጥ ስንገባ አገልግሎትም ሆነ ክርስትና ዳገት መሆኑ ቀርቶ ቀላል ይሆናል። ይህ

ማለት ግን ተግዳሮት አይኖርም ማለት አይደለም። በዚህ በመጨረሻዉ ዘመን

የምንገኝ አማኞች የበለጠ የጌታን ክብር እና መገኘት ልንጠማ ያስፈልጋል።

ምክንያቱም ዘመኑ ክፉ ስለሆነ በሰዉ የስጋ ጥበብ የምንኖርበት ሳይሆን የግድ የጌታን

ልዩ መገኘት ልንጠማ እና ልንፈልግ ያስፈልጋል። ሙሴ የጌታን ክብር በጣም

የሚጠማ እና የሚፈልግ ሰዉ ነበር። ዘጸ 32 ላይ አንተ ካልወጣህ አታዉጣን ብሎ

ጠየቀ። እግዚአብሔር ግን መልአኬን እልክልህአለሁ ሲለዉ ሙሴ አልተስማማም።

Page 22: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

22

እኔ የምፈልገዉ መልአክ ሳይሆን አንተን ራስህን መገኘትህን እፈልጋለሁ አለ።

እግዚአብሔርም በመገኘቱ ዉስጥ አድርጎ ሙሴን ይመራዉ ነበር ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- በግል ሕይወታችን የጌታ ህልዉና ከእኛ ጋር እንዲሆን

- በማያምኑ ዘንድ የጌታ ህልዉና ከእኛ ጋር እንዳለ እስኪታወቅ ድረስ

እንዲሆን

- እዉነተኛ ፀፀት እና መመለስ የሚያደርግ የጌታ ክብር እንዲታይ

- የከበረዉን ከተዋረደዉ እንድንለይ የሚያደርግ የጌታ ክብር እንዲመጣ

- በመጭዉ ኮንፍረንስ የጌታ ክብር እንዲገለጥ

አስራ አንደኛ ቀን:- በመንፈስ ቅዱስ መነቃቃት እና የጸጋ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስራት

እንዲሆን

የንባብ ክፍል ሐዋ ምዕራፍ 1- ምዕራፍ 5

መቼም መነቃቃት ወይንም ሪቫይቫል የሚባለዉን ነገር ሰዉ የሚያመጣዉ ወይንም

የሚያመነጨዉ አይደለም። በመንፈሳዊ ሰዎች ወይንም በተማሩ ሰዎች እጅ

አይደለም። የመንፈሳዊ መነቃቃት ምንጩ ራሱ እግዚአብሔር ብቻ ነዉ። አንድ ሰባኪ

እንዲህ ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ “ማዕበሉን ማምጣት አንችልም ፤ ማዕበሉ ሲነሳ

ወይንም ሲመጣ ግን እንዴት ሰርፍ ማድረግ (አብረን መትመም) እንዳለብን ማወቅ

አለብን” ሲል ሰምቻለሁ። በእርግጥ መነቃቃትን ማምጣት ባንችልም መነቃቃት

ወይንም ሪቫይቫል እንዲመጣ ግን መጸለይ እና በጸሎት መጠበቅ ግን ይጠበቅብናል።

የሐዋሪያትን ሕይወት ስናይ መነቃቃትን በጸሎት እየተጠባበቁ ነበር (ሐዋ 1፤14፣ 2፤1-

4)። በዓለ ሐምሳ የተከሰተዉ በጸሎት ሆነዉ ሲጠብቁ ነዉ። ዛሬም ተኝተን ሳይሆን

Page 23: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

23

በጸሎት ሆነን መጠበቅ ይጠበቅብናል። መቼም እዉነተኛዉን መነቃቃት ከሃሰተኛው

መለየት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። መጀመሪያ ሪቫይቫል ሲመጣ የሚሆነዉ ነገር ሰዎች

እያለቀሱ ንሰሀ መግባት ወደ ጌታ ዘወር ማለት እና የሚድኑ ሰዎች መጨመር ነዉ።

እንዲሁም ጌታን መራብ እና መጠማት ይበዛል። ከዚያም በመቀጠል ድንቆች እና

ታምራቶች ይሆናሉ። መቼም ቢሆን ድንቅ እና ታምራት ብቻዉን የሪቫይቫል ምልክት

ይሆናል ብዬ አላስብም። ድንቅ እና ታምራት የወንጌል ፓኬጅ እንጅ ብቻዉን ዋና

የሆነበት ጊዜ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን አናይም።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- እግዚአብሔርን የሚጠማ እና የሚራብ ህይወት እንዲበዛ

- በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በምዕመናን ሁሉ ላይ እንዲሆን

- ድንቆች እና ታምራቶች በመካከላችን እንዲሆኑ

- እዉነተኛዉ መነቃቃት በመካከላችን እንዲሆን

- ወንጌል በኃይል እና በስልጣን እንዲሰበክ

አስራ ሁለተኛ ቀን፦ እዉነተኛ የጸጋ ስጦታዎች በቤተክርስቲያን በሙላት እንዲሰሩ

የንባብ ክፍል 1ኛ ቆሮ 12 1ኛ ቆሮ14 ሮሜ 12

መቼም የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ጥቂቶች ተዋናይ የሚሆኑባት ሳትሆን ሁሉም

የአካሉ ክፍል ለመንግስቱ ስራ የሚንቀሳቀስበት ነች። የዳነ ሰዉ ወይንም አማኝ ተብሎ

ጸጋ ያልተሰጠዉ የለም ሁሉም አማኝ የጸጋ ስጦታ ተሰጥቶታል። ምን እንደተሰጠዉ

ግን መለየት እና ማወቅ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም አንድ አይነት ጸጋ የለም። ቃሉ ጸጋ

ልዩ ልዩ ነዉ መንፈስ ግን አንድ ነዉ ይላልና። ስለዚህ ሁሉም ምዕመናን በተሰጣቸዉ

ጸጋ እንዲያገለግሉ እና ሁሉ ጸጋዎች በሙላት እንዲሰሩ መጸለይ እና ሰዎችን ማነሳሳት

Page 24: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

24

ያስፈልገናል። ለዚህ ነዉ ጳዉሎስ ለጢሞቴዎስ “ባንተ ያለዉን ጸጋ እጆቼን በመጫን

አነሳሳለሁ” የሚለዉ (2ኛ ጢሞ 1፤6)። ሌላዉ አብረን ልንገነዘበዉ የሚገባ ነገር የጸጋ

ስጦታ በነጻ የሚገኝ ነዉ። ከሰዎች ማንነት የተነሳ የሚሰጥ አይደለም። ሁለተኛዉ ነገር

የጸጋ ስጦታ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ነዉ። እኛን ለማክበር ወይንም ለማበልጸግ

የተሰጠ ሳይሆን የክርስቶስን ሙሽራ (ቤት ክርስቲያንን) ለማሳመር እና መንግስቱን

ለማስፋት የተሰጠ ነዉ። ስለዚህ ስንጸልይም በዚህ መንፈስ መጸለይ አለብን።

ባለፈዉ ክረምት ኢትዮጵያ ሄጄ በነበር ጊዜ አንድ አገልጋይ እንዲህ ብሎ ተናገረ

“ምናለ እግዚአብሔር የፈዉስ ስጦታ በሰጠኝ እና ይሄን የኑሮ ድህነቴን ባራገፍሁት”

አለ። አንዳንዶቹ በተሳሳተ መንገድ የጌታን ጸጋ ይመኙታል። ጸጋዉ ለቤተ ክርስቲያን

የተሰጠ ነዉ ተጠቃሚዉም የእግዚአብሔር ህዝብ ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- ሁሉም የጸጋ ስጦታዎች በሙላት በቤተክርስቲያን እንዲሰሩ

- ምዕመናን ሁሉ የተሰጣቸዉን ጸጋ በተግባር እንዲያዉሉ

- እዉነተኛ የኃይል ጸጋዎች እንዲሰሩ

- የጸጋ ስጦታዎች ለተሰጡበት ዓላማ ብቻ እንዲዉሉ

አስራ ሶስተኛ ቀን፦ በሎስ አንጀለስ ያለዉ ክፉ መንፈስ እንዲመታና ከተማዋን አሳልፎ እንዲሰጠን

የንባብ ክፍል፦ ኤፌ 6፤10-18፣ 1ኛጴጥ 5፤5-8

የእግዚአብሔር ቃል ኃይለኛዉን ሳያስሩ ወደ ኃይለኛዉ ቤት ገብቶ መበዝበዝ

እንደማይቻል ይናገራል። ዲያቢሎስን በሁለት አይነት መንገድ ልንቃወመዉ

እንደሚገባ የጌታ ቃል ይነግረናል። አንደኛ ከዲያቢሎስ ወይንም ከክፉ ስራ ጋር

Page 25: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

25

ባለመተባበር እንቃወመዋለን። “ዲያቢሎስን ተቃወሙት ከእናንተም ይሸሻል ወደ

እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” እንደሚል ቃሉ። ሁለተኛዉ ወደ

እግዚአብሔር በመቅረብ በጸሎት እንቃወመዋለን። እኛ ወደ እግዚአብሔር በቀረብን

ቁጥር ዲያቢሎስን እየተቃወምን እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። በኢየሱስ ስም ብለን

ብንገስጽም ባንገስጽም ወደ እግዚአብሔር መቅረባችንና ጸሎት ማብዛታችን፤ ጌታንም

አብዝተን መዉደዳችን የዲያቢሎስን ስራ ያፈርሳል። የኤፌሶንም ጸሐፊ በኤፌ6፤10-17

መጋደላችን ከደም እና ከስጋ ጋር ስላልሆነ ታጠቁ ነዉ የሚለን። ሌላዉ የጽድቅ ልብስ

መልበሳችን የዲያቢሎስን ስራ ያፈርሳል። ክርስቶስ ልብሳችን ሆኖ በወንጌል እዉነት

ስንቆም ዲያቢሎስ መግቢያ ነዉ የሚያጣዉ። ብዙ ጊዜ በህይወት ከመዋጋት ይልቅ

በአፍ መዋጋትን እናስቀድማለን። በአፍ ብቻ የምናደርገዉ ዉጊያ ዲያቢሎስን ፈጽሞ

አያስደነግጠዉም፤ ምናልባትም ይስቅ ይሆናል ። ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ ልንዋጋዉ

ይገባል ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- በከተማዉ ላይ የሚሰራዉ የክፉ ኃይል እንዲመታ

- አማኞች በአንደበት ብቻ ሳይሆን በሕይወት የምንዋጋበት አቅም እንዲሰጠን

- በከተማዉ የሚሰራዉ የግብረ ሰዶማዊነት መንፈስ እንዲመታ

- ወንጌል በኃይል እንዳይሰበክ የሚቃወም ተቃዋሚ መንፈስ እንዲመታ

- የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስና መስቀል አልባ እምነት እንዲመታ

አስራ አራተኛ ቀን፦ እያንዳንዳችን የየራሳችንን ኢየሩሳሌም በወንጌል መድረስ እንድንችል

የንባብ ክፍል፦ ሐዋ 1፤8፣ ሮሜ 9፤1-13

Page 26: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

26

መቼም ወንጌል የሚጀምረዉ ከቤት ነዉ። ከቤት ያልጀመረ ነገር ሁሉ ትክክል

አይሆንም። ሐዋሪያትን ኢየሱስ ሲልካቸዉ መጀመሪያ ከኢየሩሳሌም ከከተማቸዉ

ከጎረቤታቸዉ እንዲጀምሩ ነዉ ያዘዛቸዉ። የቤቱን ከደረስን በኋላ ነዉ ወደ ዉጭ

መዉጣት የምንችለዉ (ሐዋ 1፤8)። ሐዋሪያዉ ጳዉሎስ ሲናገር ስለ እስራኤላዊያን

ዘመዶቹ እነርሱ የማይድኑ ከሆነ በስጋ ዘመዶቼ ስለሆኑ ስለ ወንድሞቼ ከክርስቶስ

ተለይቼ እኔ እራሴ የተረገምሁ እንድሆን እጸልይ ነበርና ይላል (ሮሜ 9፤3)።

ሐዋሪያዉ ጳዉሎስ ምን ያህል ሀዘንና ጭንቀት ስለ ጠፉ ዘመዶቹ እንደነበረበት

ይናገራል። ዛሬ በእዉነት እኛ ስለሚጠፉ ዘመዶቻችን ምን ያህል እናስባለን?

በጸሎታችንስ ምን ያህል እናስባቸዋለን? ካለመዳን አለመፈጠር ይሻላል። በእዉነት

ከልብ በእንባ ልንጸልይላቸዉ እና ወንጌልን ባለመሰልቸት ልንነግራቸዉ ይገባል ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- የየራሳችንን ኢየሩሳሌም (ቤተሰቦቻችንን) መድረስ እንድንችል

- ላልዳኑ ዘመዶቻችን እዉነተኛ ሸክም እንዲሰማን

- ወንጌል የምንናገርበትን ጥበብ ጌታ እንዲሰጠን

- ዘመዶቻችንን እንዲያወርሰን

አስራ አምስተኛ ቀን፦ ሎስ አንጀለስ እና አካባቢዉን ጌታ አሳልፎ እንዲሰጠን

የንባብ ክፍል ማቴ 28፤18-20 ማር 16፤8-15

ለሎስ አንጀለስ ለብዙ ዘመናት እንደተጸለየ ሁላችንም እናዉቃለን። ነገር ግን በጸሎት

መታከት እንደሌለብን የእግዚአብሔር ቃል ስለሚነግረን አሁንም ሳንታክት መጸለይ

ኖርብናል።

Page 27: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

27

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- ሎስ አንጀለስ እና አካባቢዉን አሳልፎ እንዲሰጠን

- ያልዳኑ እንዲድኑ

- ወንጌል በሙሉነት እንዲሰበክ

- የሚድኑትን የምንይዝበት ጸጋ እንዲጨመርልን

አስራ ስድስተኛ ቀን፦ ለልጆች እና ለትዉልዱ

የንባብ ክፍል ኤር 33፤1-3፣ ማቴ 18፣ ዘጸ 1

ልጅህን በሚሄድበት መንገድ ምራዉ ከእርሱም ፈቀቅ አይልም (ምሳ 22፤6)

እንደሚል የእግዚአብሔር ቃል ልጆችን ከዚህ ክፉ ነገር አስመልጦ የእግዚአብሔርን

መንግስት የሚያሰፋ ትዉልድ ማፍራት ይጠበቅብናል። የኤሊ ልጆች ምናምነቴዎች

ነበሩና የእግዚአብሔርን ስራ ይዘዉ ሊቀጥሉ አልቻሉም። ትልቁ ችግር የነበረዉ ልጆቹ

ላይ ሳይሆን ችግሩ አባታቸዉ ላይ ነበር። ለእነርሱ የወደፊት መንፈሳዊ ህይወት ግድ

የለሽ ነበር። ዛሬም ለሚቀጥለዉ ትዉልድ የምናስብ ከሆነ ልጆች ላይ ወይንም

ትዉልዱ ላይ ስራ መሰራት ይኖርበታል። ልጆቻችንን ከዚህ ክፉ ዘመን ጠብቀን

በእግዚአብሔር እዉነት ለማሳደግ እና በሚቀጥለዉ ትዉልድ የእግዚአብሔርን

መንግስት የሚያሰፋ ኃላፊነት የሚቀበል ትዉልድ ለማፍራት በእግዚአብሔር ፊት

በጾም እና በጸሎት መትጋታችን ኪሳራ ሳይሆን ትልቅ ትርፍ ነዉ።

Page 28: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

28

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- እግዚአብሔር ልጆቻችንን ከዚህ ክፉ ትዉልድ እንዲታደጋቸዉ

- በዘመናቸዉ እና በትዉልዳቸዉ ለዉጥ እና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ እንዲሆኑ

- ልጆችን በትክክለኛ መንገድ የመምራት ጥበብ እና ኃይል ከእግዚአብሔር

ዘንድ እንዲሰጠን

- ትዉልዱን የሚገዳደረዉን ክፉ ጌታ እንዲመታ

- እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሌላዉን የሚያከብር፣ ኃጢአትን የሚጸየፍ

ትዉልድ እንዲፈጠር

አስራ ሰባተኛ ቀን፦ ስለ ስለ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት ያለዉን ግራ መጋባት ጌታ እንዲያጠራ

የንባብ ክፍል፦ ማቴ 16፤18፣ ሐዋ 4

በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያንን የሚገጥሟት ተግዳሮቶች ቀላል አይደሉም። ነገር ግን

እዉነተኛዋን ቤተ ክርስቲያን የገሀነም ደጆች ስለማይችሏት ተግዳሮቶቹን ሁሉ

እየጣሰችና እያሸነፈች መሔዷ የማይቀር እዉነት ነዉ። ቤተ ክርስቲያን ከተኛችበት

ነቅታ የዘመኑን የጌታን ሀሳብ በመረዳት የተሰጣትን ተልዕኮ እንድትወጣ መጸለይ

ያስፈልጋታል። የመጀመሪያዋ ቤተክርሰቲያን ትልቁ ችሎታዋ በእግዚአብሔር ፊት

በጸሎት መትጋቷ ነበር። በመካከላቸዉ የነበረዉ ድንቅ እና ተዓምራት እንዲሁ

በምትሀት አልመጣም። በየእለቱ ከጌታ ጋር በሚያደርጉት ትጋት የመጣ ነበር።

በተለይም ኢትዮጵያ ዉስጥ ላለችዉ ቤተ ክርስቲያን መጸለይ ያስፈልገናል። አሁን

ባለዉ እንቅስቃሴ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ነገር እየመጣ ስላለ ጌታ

ቤቱን እንዲያጠራና ትክክለኛውን ነገር እንዲያመጣ መጸለይ ያስፈልጋል።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

Page 29: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

29

- በዚህ ዘመን የተነሳዉን እንቅስቃሴ ጌታ እንዲያጠራ

- ሐሰተኞች ከእዉነተኞች እንዲለዩ

- በዚህ እንቅስቃሴ ዉስጥ እዉነተኞች አብረዉ እንዳይጉዱ ጌታ እዉነተኞችን

እንዲጠብቅ

- ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዋን እንድትወጣ

አስራ ስምንተኛ ቀን፦ ስለ ሃገራችን ኢትዮጵያ

የንባብ ክፍል፦ 2ኛ ጢሞ 2፤1-5፣ ነህ 1፣ 1ኛ ዜና 4፤8-10

በአሁኑ ጊዜ ሃገራችን ኢትዮጵያ በብዙ ሁኔታ ጸሎት ያስፈልጋታል። በኢኮኖሚዉም

ሆን በፖለቲካዉ ብዙ ችግሮች አሉ። በምድሪቱ ላይ ሀብታሞች ቢኖሩም በቀን አንድ

ምግብ ለመብላት የሚቸገሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸዉ። በሃገሪቱ ላይ ያለዉ የዘር

መከፋፈል እንዲሁም በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለዉ አለመግባባት እንዲጠፋ

ልንጸልይ ያስፈልጋል። ስለ ሃገራችን ስንጸልይ በብዙ መረዳትና ጥበብ ወደ

እግዚአብሔር እንድንጮህ ያስፈልጋል። ኤር 33፤3 እግዚአብሔር ኤርምያስን “ወደ

እኔ ጩህ እኔም እመልስልሃለሁ አንተም የማታዉቀዉን ታላቅ እና ኃይለኛ ነገር

አሳይሃለሁ” ብሎታል። እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ጩኸታቸችንን እንደሚሰማ

እና እንደሚመልስ በማመን መጮህ ያስፈልጋናል ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- በሀገራችን ህዝቦች መካከል እዉነተኛ ሰላም እና ፍቅር እንዲሰፍን

- በመንግስት እና በህዝቡ መካከል መከባበር እንዲሆን

Page 30: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

30

- ሙስና፣ አድሎ፣ ዘረኝነት ከምድራችን እንዲወገድ

- በምድራችን ያሉ ችግረኞች ጌታ እንዲያስባቸው

- ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት ከምድራችን እንዲወገድና ተፋቅሮና ተሳስቦ

መኖር እንዲሆን

- በወቅቱ ያሉ መሪዎችን እግዚአብሔር ማስተዋል እና ጥበብ

እንዲጨመርላቸዉ።

- ደም መፋሰስ እና ክፉ ነገር እንዲወገድ

አስራ ዘጠነኛ እና ሃያኛው ቀን፦ በፊታችን ስለሚመጣዉ አመት 2018

የንባብ ክፍል ኤፌ 5፤14-18፣ ዮሐ 17፤1-26

ኤፌ 5፤15-16 እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጅ ጥበብ እንደሌላቸዉ ሳይሆን እንዴት

እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸዉና ዘመኑን ዋጁ ይላል።

ዘመንን መዋጀት ማለት ጊዜን በአግባብ መጠቀም ማለት ነዉ። በዚህ ምድር

የምንኖረዉ ኑሮ አጭርና ዉስን ነዉ። ሆኖም ግን ትልቁ ወይንም ከቁጥር በላይ

የሆነዉን ዘላለማችን የሚወስነዉ ደግሞ በዚህ አጭር ዘመን የምናደርገዉ ዉሳኔ ነዉ።

ለዚህ ነዉ በጥንቃቄ እንደ ጥበበኞች መኖር ያለብን። በሐዋ 13፤36 “ዳዊት በራሱ

ዘመን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ” ይላል። ዳዊት በራሱ ዘመን

የማንንም ሃሳብ ሳይሆን የአምላኩን ሃሳብ እና ፈቃድ አገልግሎ አለፈ።

የእግዚአብሔርን ሃሳብ ማገልገል ማለት በብዙ የአገልግሎት ዘርፍ ገብቶ ስራ-በዝ

መሆን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሃሳብ ማገልገልና ለዘመኑ እና ለጊዜዉ የሚሆነዉን

የእግዚአብሔርን ሃሳብ መረዳት ማለት ነዉ። የይሳኮር ልጆች ሃያላን የነበሩ፣ ግን

ዘመኑን ያወቁ ነበሩ። ሃያላን ያሰኛቸዉ የጊዜዉን ሃሳብ በመረዳት ያገለግሉ ስለነበር

Page 31: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

31

ነዉ (1ኛ ዜና 12፤32)። እኛም የጊዜዉን ሃሳብ በመረዳት በዚህ ጊዜ ምን እንድናደርግ

ነዉ የሚፈልገዉ ብሎ በመረዳት እንድናገለግልና በእግዚአብሔር ፊት በጾም እና

በጸሎት መቅረባችም መልካም ነዉ። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲፈጽም እንዲህ ብሎ

ነዉ የጸለየዉ። “የሰጠህኝን ፈጽሜ አከበርሁህ”። የተሰጠዉን ብቻ በመረዳት እርሱን

ነዉ የፈጸመዉ። የተገኘውን ሁሉ ስራ መስራታችን ሳይሆን ቁልፉ ነገር የተሠጠንን

ተረድተን ፈጽመን ማለፋችን ነዉ። አሁንም በመጭዉ ዘመናችን ዘመኑን እየዋጀን

የተሰጠንን እየፈጸምን እንድንሄድ መጸለይ አስፈላጊ ነገር ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- መጪዉ አመት ያገኘነዉን የምንሰራበት ሳይሆን የእርሱን ፈቃድ

የምንፈጽምበት እንዲሆን

- ብዙ ሰዎች የሚድኑበት አመት እንዲሆን

- ዘመኑን እየለየን መጓዝ እንዲሆን

- የአገልግሎት ዘርፎች ሁሉ ያቀዱትን እና ከዚያም በላይ መፈጸም እንዲሆን

ሃያ አንደኛ ቀን፦ የምስጋና ቀን

የንባብ ክፍል ራዕ 4፤11፣ ራዕ 5፤7፣ ዘጸ 1፤1-15፣ 1ኛ ሳሙ 2 በሙሉ

በምስጋን ጀምረን በምስጋና መጨረስ አለብን። ይህ ቀን እነዚህን ሁሉ ቀናት በፊቱ

እንድንሆን ለረዳን ለአምላካችን ምስጋና እና አምልኮ የምናቀርብበት ቀን ይሆናል።

መጀመሪያ እንደተገለጸው ምስጋና የህይወታችን ክፍል መሆን አለበት። አንድ ነገር

ተጀምሮ እንዲያልቅ የሚረዳ እግዚአብሔር ስለሆነ ልናመሰግነዉ ይገባል።

እስራኤላዊያንን ቀይ ባህርን ከፍሎ ሲያሻግራቸዉ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር

Page 32: የሃያ አንድቀን ጾምእናጸሎት · 2017-12-05 · 3 የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተ ክርስቲያን ሎስ አንጀለስ አንድቀንየሃያ

32

ዘምረዋል። ዘጸ 15፤2-3 ላይ “ይህ አምላኬ ነዉ አመሰግነዉማለሁ፤ የአባቴ አምላክ

ነዉ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ እግዚአብሔር ተዋጊ ነዉ ስሙም እግዚአብሔር ነዉ”

በማለት በማሪያም መሪነት ጌታን ያመሰግኑ ነበር። ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች

በሕይወታቸዉ ላይ አንድ ነገር ከሆነ በኋላ ያመሰግናሉ። ኢዮብም ከዚያ ሁሉ መከራ

በኋላ “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ ሃሳብህም እንደማይከለከል አወቅሁ”

ብሏል ። (ኢዮ 42፤2)። ሐናም ሳሙኤልን በጸሎት ከወለደች በኋላ እንዲህ እያለች

አመስግናለች “ቀንዴ ከፍ ከፍ አለ አፌም በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ በማዳንህ ደስ

ብሎኛል፤ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና እንደ አምላካችን ጻድቅ የለምና ከአንተ

በቀር ቅዱስ የለም (1ኛ ሳሙ 2፤1-2)። እግዚአብሔር ልመናዋን ሰምቶ ልጅ ስለ ሰጣት

ከልብ የሆነ ምስጋና አቅርባለች። እግዚአብሔር ስላደረጋቸዉ መልካም ነገሮች ሁሉ

ማመስገን እና ማድነቅ ይኖርብናል። ሊመሰገን የሚገባዉ አምላክ ስለ ሆነ በሰማይ

ያሉ ሰራዊት ሁሉ ስራቸዉ ይገባሀል እያሉ መስገድ ነዉ።

የእለቱ የጸሎት ትኩረት

- ጌታ ስለ ረዳን ማመስገን

- ስለ ታላቅነቱ እና ስለ አባትነቱ ማድነቅ

- በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ጌታ ስለረዳን ማመስገን

- አመቱን በሙሉ የጌታ እጅ ከእኛ ጋር ስለነበር ምስጋና ማቅረብ

- 2018ን ጌታ አሳልፎ ስለሚሰጠን በማመን ማመስገን

***

የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ህብረት ቤተክርስቲያን ሎስ አንጀለስ የጸሎት አገልግሎት ክፍል

December 2017